
የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት ዝግጁነት ግምገማ በስኬት ተጠናቀቀ
መቐለ፣ ግንቦት 30/2018 – በመቐለ ዩኒቨርሲቲ በሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የራስ ገዝነት ዝግጁነት ግምገማ በስኬት መጠናቀቁን በትምህርት ሚኒስቴር የተሰየመው የግምገማ ቡድን ለዩኒቨርሲቲው ማናጅመንት ባቀረበው የመውጫ ኮንፈረንስ አስታወቀ።
ከዚህ በፊት እንደተገለጸው፣ የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በቀጣይ በጀት ዓመት የራስ ገዝ (Autonomous) አስተዳደር ስርዓት ለመመሰረት ሂደቱን ከጀመሩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል መቐለ ዩኒቨርሲቲ አንዱ መሆኑ ይታወቃል። በዚሁ መሰረት የተላከው የባለሙያዎች ቡድን በዩኒቨርሲቲው የነበረውን የሶስት ቀን የዝግጁነት ግምገማ አጠናቆ የመውጫ ሪፖርቱን አቅርቧል።


የግምገማ ቡድኑ በቆይታው ላለፉት ቀናት በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጁ ሰነዶችን መርምሯል። በተጨማሪም ላብራቶሪዎችን፣ ወርክሾፖችን፣ የምርምር ማዕከላትን፣ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም የልማት ስራዎችን በአካል ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ከመምህራን፣ ተማሪዎች፣ ሰራተኞች እና ተወካዮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
በመውጫ ሪፖርቱ ላይ እንደተመላከቸው ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ሚኒስቴር በተዘጋጀው የዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝ ዝግጁነት ግምገማ መስፈርት መሰረት መካሄዱን የተገለፀ ሲሆን የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ጠንካራ ጎኖችና መሻሻል ያለባቸው ነጥቦች ተመላክቷል። የቡድኑ አባላት በቆይታቸው በዩኒቨርሲቲው የግምገማው ሂደት የተሳካ ከማድረግ አዃያ ላደረገላቸው ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋና ሓጎስ በበኩላቸው ለቡድኑ አባላት በቀረበው ገንቢ ሪፖርት ምስጋና አቅርበው፣ ሪፖርቱ ለቀጣይ ምን መስራት እንዳለብን ለመለየት የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው የተገለጹትን ጥንካሬዎች ይበልጥ በማጠናከር መሻሻል ያለባቸውን ክፍተቶች ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ገብተን እንደሚያስተካክል በቁርጠኝነት ተናግረዋል።
በቀጣይ የግምገማ ቡድኑ በግምገማ መስፈርቱ መሰረት የሚሰጠውን ውጤት ለትምህርት ሚኒስቴር እንደሚያስረክብ ይጠበቃል።
